1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

https://p.dw.com/p/4fg9t

በሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ተሰደው አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር  ዞን ተጠልለው የነበሩ  1 ሺ 300 ገደማ ያህል ስደተኞች መጠለያ ጣቢያውን ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ተናገሩ።

ስደተኞቹ ከመጠለያ ጣቢያቸው ለመልቀቅ የምግብ አቅርቦት እና የጸጥታ ችግርን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት በበኩሉ ለስድተኞቹ ተገቢው ጥበቃ እየተደረገላቸው በመሆኑ ከመጠለያ ጣቢያው መውጣት አልነበረባቸውም ብሏል።

መጠለያ ጣቢያውን ለቀው ከወጡት ውስጥ አንዱ በተለይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት «ለጥያቄያችን ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘታችን መጠለያውን ለቀን ለመውጣት ተገደናል » ብለዋል።

“ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የምንፈልገው ነገር ነበር፣ አሁን ያለንበት አውላላ ሰው የሚሰፍርበት ኤደለም ለምን አሁን መፍትሔ አይፈለግለትም፣ የምግብ እጥረትም ነበረ፣ የፀጥታ ችግርም አለ በሚል ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡”

የጸጥታ ችግር አጋጥማናል በሚል ከ 1 ሺ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች ከመጠለያ ጣቢያቸው መውጣታቸውን ያየዓለም ዋጭ፣ የኩመርና የአውላላ ጣቢያዎች የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ታምራት ደምሴ አረጋግጠዋል። ነገር ግን አስፈላጊው የፀጥታ ሥራ እየተሰራ በመሆኑ ስደተኞቹን ወደ መጠለያቸው ለመመለስ እየተሰ,ራ ነው ብለዋል።

“ ከዋናው መጠለያ ወደ አንድ ኪሎ ሜትር አካባቢ ወደ ጎንደር እንሄዳለን ብለው ወጥተዋል፣ ለምን ሲባሉ የፀጥታ ችግር አለ ይላሉ፣ ፌደራል ፖሊስ አለ፣ የአገር መከላከያ አለ፣ ተመለሱ ፀጥታውን እናስጠብቃለን ብለናል፣»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያመለክተው በአማራ ክልለ ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ8 ሺ 500 በላይ የሱዳን ፣ ደቡብ ሱዳን እና የኤርትራ ስደተኞች ይገኛሉ ።

 

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ታዬ ደንደአ በማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ብይን ሰጠ፡፡

ፍርድ ቤቱ በተከሳሹ ጠ,በቆች የቀረቡለትን የዋስትና ጥያቄዎች ሳይቀበለው ቀርቷል። የፍትህ ሚኒስቴር በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተጠቀሰውን ድንጋጌ በመተላለፍ በአቶ ታዬ ላይ ሶስት ተደራራቢ ክሶች አቅርቧል። በክሱ ከተዘረዘሩት ውስጥ የጦር መሳሪያ አዋጅን መተላለፍ፤  የተጣለባቸውን መንግስታዊ ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በስማቸው በተከፈተ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የጸረ ሰላም ኃይሎችን የሚደግፉ መልዕክቶችን ማሰራጨት ይገኙባቸዋል።

ከአቶ ደንደአ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ለዶቼ ቬለ እንዳሉት በተከሳሹ ላይ የቀረበው ክስ  ተደራራቢ መሆኑንና ክሶቹ ከፍ ያለ ቅጣት የሚስቀጡ በመሆኑ የዋስትና ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም ። በዚህም አቶ ታዬ ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱን ነው ጠበቃው የተናገሩት ።

አቶ ታዬ በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ እና ዐቃቤ ህግ በሰጠው የጽሁፍ ምላሽን መርምሮ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን የአዲስ አበባው ወኪላችን ስዩም ጌቱ ዘግቧል። የምሽቱ መጽሄተ ዜናችን በዚህ ጉዳይ ላይም ዝርዝር ዘገባ ይዟል።

 

ዓለማቀፉ የሰብአዊ መብት ተመልካቹ ቡድን ሁማን ራይትስ ዎች አር ኤስ ኤፍ የተሰኘው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ቡድን እና አጋሮቹን በዳርፉር የዘር ማጽዳት ወንጀል ከሰሰ ።

የሰብአዊ መብት ተመልካቹ ቡድን ዛሬ ባወጣው መግለጫው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በምዕራብ ዳርፉር በማሳሊት ጎሳ አባላት ላይ እየፈጸመ ያለው የጅምላ ግድያ መጠን «የዘር ማጥፋት » ሊሆን ይችላል።

በምዕራብ ዳርፉር ግጭት ከተቀሰቀሰበት ከጎርጎርሳውያኑ የሚያዝያ  እስከ ሰኔ 2023 ድረስ የአር ኤስ ኤፍ ኃይሎች ከአካባቢው የአረብ ሚሊሻዎች ጋር በመቀናጀት የማሳሊት ጎሳ አባላት በሚኖሩበት ኤል ጄኒና መንደሮች ላይ ተከታታይ ጥቃት መድረሱ በሪፖርቱ ተመልክቷል። ይህንኑ ተከትሎ በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የተፈናቃይ የማሳሊት ጎሳ አባላት የጅምላ መቃብር መገኘቱንም የፈረንሳይ እና የጀርመን ዜና አገልግሎቶች ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ባለፈው የህዳር ወርም በተመሳሳይ በተመሳሳይ ብርቱ ግጭት መቀስቀሱን የጠቀሰው የመብት ተሟጋቹ ቡድን መግለጫ በማሳሊት ጎሳ አባላት ላይ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ የአካል ስቅየት እና የተቀናጀ ዘረፋ መፈጸሙን አረጋግጧል።

በሰሜን ዳርፉሯ ኤል ፋሽር ዉጊያ ተባባሶ መቀጠሉን የጠቀሰው ሁማን ራይትስ ዎች ከተማዋ የበርካታ ተፈናቃይ ሱዳናውያን መገኛ እንደመሆኗ የመንግስታቱ ድርጅት ጣልቃ ገብቶ እንዲከላከል ጠይቋል። አስር ሺዎችን ለህልፈት ፤ ሚሊዮኖችን ለስደት የዳረገው እና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል እና ብሄራዊ ጦር መካከል የሚደረገው ጦርነት ከአንድ ዓመት በላይ አስቆጥሯል።

 

ሁለት ወራት ገደማ ያስቆጠረው የኬንያ የመንግስት ሆስፒታሎች ሐኪሞች የስራ ማቆም አድማ አበቃ ።

ሀኪሞቹ ከኬንያ መንግስት ጋር ከስምምነት መድረሳቸውን ተከትሎ ብሄራዊ የስራ ማቆም አድማቸውን መግታታቸውን አስታውቀዋል።

ደካማ የክፍያ ስረዓትን ጨምሮ የስራ ማቆም አድማ ያስከተሉ ጉዳዮችን ጨምሮ የተነሱ ችግሮችን ለመፍታት ከስምምነት በመደረሱ ሀኪሞቹ ወደ ስራ መመለሳቸውን ሰራተኛ ማህበሩ ዋና ፀሀፊ  ዳቭጂ አቴላ ተናግረዋል።

 ጉዳዩን የተመለከተው የሀገሪቱ ፍርድቤት መንግስት እና ሀኪሞቹ ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ እንዲያበጁ ባለፈው ማክሰኞ  የ48 ሰዓታት ጊዜ ሰጥቷቸው ነበር።

የሐኪሞቹ የስራ ማቆም አድማ ዕልባት ማግኘቱ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኬንያውያን እፎይታ አስገኝቶላቸዋል።

ለሁለት ወራት የዘለቀው የሀኪሞቹን የስራ ማቆም አድማ ተከትሎ በርካታ ሆስፒታሎች በጊዜያዊነት አዳዲስ ሀኪሞች እስከመቅጠር ደርሰው እንደነበር የአሶሽየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል።

ኬንያ በአሁኑ ወቅት ብርቱ የጎርፍ መጥለቅለቅ ካደረሰባት ብርቱ ጉዳት ለማገገም እየተጣጣረች ትገኛለች። አደጋው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለህልፈት ዳርጎ ከ235 ሺ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለጉዳት ዳርጓል።  

 

በደቡብ አፍሪቃ ጆርጅ ከተማ ውስጥ በተናደ ህንጻ ፍርስራሽ ስር ከተቀበሩ አራተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩ የ44 የግንባታ ሰራተኞችን በህይወት ለማግኘት ተስፋቸው እየተመናመነ መምጣቱን ቤተሰቦቻቸው ተናገሩ ።

 ፍርስራሾቹን በማንሳት ላይ የሚገኙ ግዙፍ ማሽነሪዎች በፍርስራሾች ስር የሚገኙትን ሰዎች ለማትረፍ አልፈጠኑም ሲሉም ከሰዋል። ባለፈው ሰኞ በ81 ሰዎች ላይ በተደረመሰው ባለ አምስት ፎቅ ህንጻ የ29 ሰዎች ህይወት ወዲያው ሲያልፍ 16 ሰዎች በህይወት ተርፈው በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የከተማዪቱን ማዘጋጃ ቤት ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

በአደጋው እስካሁን ድረስ እንደተቀበሩ የሚገኙ ሰዎች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሚሰራጨው መረጃ ባሻገር ማንነታቸውም ሆነ ዜግነታቸው  አሁንም ድረስ በመንግስት ይፋ አልተደረገም።

የህይወት አድን ሰራተኞች ከህንጻ ፍርስራሾች ስር የሰዎች ድምጽ ይሰሙ እንደነበር ቢገለጹም ከዚያ በኋላ ስላለው ተጨባች ሁኔታ የታወቀ ነገር አለመኖሩን ዘገባው አመልክቷል።  

ለህንጻው መደርመስ ምክንያት ለጊዜው አልታወቀም ።ነገር ግን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ምርመራ እንዲደረግ አዘዋል።  

 

 

የእስራኤል ወታደሮች በራፋህ በመኖሪያ አካባቢዎች በታንክ የታገዘ ጥቃት መክፈታቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ ።

የእስራኤል በራፋህ ጥቃት መክፈት የተሰማው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እስራኤል በራፋህ ወረራ ከፈጸመች የሚቀርብላት የጦር መሳሪያ ድጋፍ የተወሰነውን እንደሚገቱ ካስታወቁ በኋላ ነው።

በካይሮ ለድርድር የተቀመጠው የፍልስጥኤማውያኑ ታጣቂ ቡድን ሃማስ በበኩሉ ታጣቂዎቹ በራፋህ ምስራቃዊ ሸለቆ በእስራኤል ታንኮች እና ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ዘረ ታንክ ፣ ሮኬቶች እና ሞርታሮች እያስወነጨፉ እንደሚገኙ አስታውቋል።

 ማዕከላዊ የራፋ ክፍል እስካሁን በእስራኤል ወታደሮች አለመያዙን የገለጹት ነዋሪዎች እና የህክምና ምንጮች እንዳሉት የእስራኤል ታንኮች በአንድ መስጊድ አቅራቢያ ባደረሱት ጥቃት እስካሁን ሶስት ሰዎች ተገድለው ሌሎች በርከት ያሉ ሰዎች ቆስለዋል።

እስራኤል እንደምትለው የሃማስ ታጣቆዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማውያን በተጠለሉባት ራፋህ ተጠልለው ይገኛሉ ። ለዘላቂ ደህንነቴ ስል «ታጣቂዎቹን እስካጠፋ አልመለስምም» ብላለች,።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው እስራኤል በግትርነቷ ጸንታ በራፋህ ወረራ ከፈጸመች « የሚደረግላት የጦር መሳሪያ ድጋፍ ይቋረጥባታል» ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ታምራት ዲንሳ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሄር

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

ከዚሕ ዝግጅት ተጨማሪ

Äthiopien Alamata City Gondar
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።