1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ባህልሰሜን አሜሪካ

የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች የሰላም ትርዒት

ሐሙስ፣ ግንቦት 1 2016

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ያለመ የተባለ የባህል ትርዒት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሊካሄድ ነው ። አዘጋጆቹ የዚህ ትርዒት ዓላማ፥ በሰላም አስፈላጊነት እና በሕዝቦች መቀራረብ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4ffVl
 የሰላም አስፈላጊነት
የሰላም አስፈላጊነት አጽንኦት ሊሰጠው ይገባል ተብሏልምስል Fotolia/chris-m

የሕዝቦች መቀራረብና የሰላም አስፈላጊነት

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ያለመ የተባለ የባህል ትርዒት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሊካሄድ ነው ። የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ከሃገር ቤት የመጡ የባህል ባለሞያዎች የሚሳተፉበት የዚህ ትርዒት ዓላማ፥ በሰላም አስፈላጊነት እና በሕዝቦች መቀራረብ ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ።

አቶ አሉላ አንዳሉት፦ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ የዐማራና ትግራይ ሕዝቦች ከድንበር ተያይዞ በሚነሱ የይገባኛል ጥያቄዎች፣ በጋራ ተስማምተው የሚኖሩባቸው እንጂ የሚጋጩባቸው መሆን አይገባቸውም ።

የሕዝቦች መቀራረብና የሰላም አስፈላጊነት

የፊታችን ቅዳሜ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከኢትዮጵያ በመጡ በዋናነት የሁለቱ ሕዘቦች የባህል ባለሞያዎች ሊካሄድ የታቀደው የባህል ትርዒት ይህንኑ የሰላም አስፈላጊነትና የሕዝቦች መቀራረብ ለማስተጋባት ያለመ ነው ተብሏል ።

«ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ይታወቃል፥ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለችው ሃገሪቷ። ስለዚህ ሕዝቦችን በማቀራረብ በሕዝቦች መኻከል ሰላም እንዲኖር፥ ግንኙነቱ በተለይ በዲያስፖራ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ያንን ታሳቢ በማድረግ ነው።» የዝግጅቱ አስተባባሪ፦ ይኸው ትርዒት የሕዝብ ለሕዝብ የማቀራረብ  ሥራ ተገቢ ነው በሚል በሲቪል ማኀበራት የሚሰጡ መግለጫዎችን ተከትሎ የተሰናዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

የተስተዋሉ የግጭት ምልክቶች

«በተለይ አሁን በትግራይና በዐማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ወደ ግጭት ሊያመሩ የሚችሉ ነገሮችና ምልክቶች ሲታዩ ይህ መቅረት አለበት፥ በፍጹም ሕዝቦቹ በግጭት ወስጥ ሊቀጥሉ አይገባም የሚል አመለካከት ያላቸው ሰዎች በመቀራረብ የተጀመረ ነው።

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ያለመ የተባለ የባህል ትርዒት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሊካሄድ ነው
በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በሚታይባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሕዝቦችን ለማቀራረብ ያለመ የተባለ የባህል ትርዒት ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሊካሄድ ነው። የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ አሉላ ሰለሞን ምስል Tariku Hailu/DW

የዓለም አቀፍ ፍትሕ ለትግራይ መግለጫ

በሌላ በኩል፣ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ስለትግራይ ክልል፤ ስለአጎራባች ክልላዊ መንግሥታትና ስለጉዳዩ ሕገ መንግስታዊ እንዲሁም ታሪካዊ ሁኔታ ሰጡት ያለው መግለጫ እንዳሳዘነው ዓለም አቀፍ ፍትሕ ለትግራይ ማኀበር የተባለው ድርጅት ዐስታወቋል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የድርጅቱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ገብረ እግዚአብሔር፦ ስለጉዳዩ ድርጅታቸው ያወጣውን መግለጫ አስመልክቶ ጠይቀናቸው ነበር። «ከኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ጋር የሚጻረሩ ነገሮችን አንስተዋል። እና ስጋታችን የፕሪቶሪያ ሥምምነት ያመጣው ሰላም አለና፣ የእርሳቸው ሃሳብ እንደውም የመጣውን የሰላም ሂደት እሳቸውም በታዛቢነት የተሳተፉበትን የሰላም ሂደት እንዳያኮላሸውና ወደ ቅርቃር እንዳያስገባው ነው የእኛ ዋናው ስጋታችን።»

የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ጥሪ

የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ፣ የሰሜን ኢትዮጵያን ሁኔታ አስመልክተው በቅርቡ ባወጡት መግለጫ፦ አወዛጋቢ ላሏቸው አካባቢዎች ምላሽ  ለመስጠት፣ የፖለቲካ ውይይት እንዲጀመር ጥሪ አቅርበው ነበር።

የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ
የአፍሪቃ ኅብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪምስል Monasse Thierry/ANDBZ/ABACA/picture alliance

ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ግን የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት እስከተከተሉ ድረስ «አወዛጋቢ» የሚባል አካባቢ የለም ባይ ናቸው። «እኛ የክልል አከላለል ይሁን የቦታዎች ይዞታ ሕገ መንግስቱ ያስቀመጠው ነገር አለ። ሕገ መንግስቱ እስካልተቀየረ ድረስ፣ በሕገ መንግስቱ ነው መሆን ያለበትና አወዛጋቢ የሚል ነገር አይኖርም ማለት ነው። ሕገ መንግስቱን እስከተከተሉ ድረስ አወዛጋቢ የሚለውን ነገር መጠቀማቸው ራሱ ትክክል አይደለም፥ ችግርም የሚፈጥር ነው።»

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት፣ የማንነትና የወሰን ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንደሚፈታ፣ ግልጽ አቅጣጫ ማስቀመጡን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር